ከትናንት የሚልቅ ትጋትን የሚሻው ኤች አይ ቪ

ዮርዳኖስ ፍቅሩ
ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ እድገት፣ “የሰው ኃይል” ሊተካ የማይችል ወሳኝ ግብዓት ነው፡፡ የተሻለ የስልጣኔና የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሀገራት የዕድገታቸው መሠረት ዜጎቻቸው ናቸው፡፡ በዓላማ የሚተጋ ዜጋ የራሱን ነገ አሳምሮ ይሠራል፤ ከራሱ አልፎ ለቤተሰቡ፣ ማኅበረሰብና ሀገሩ የተሻለ ሐሳብን ከማፍለቅ ጀምሮ ባለው አቅም ሁሉ ያለውን ለመስጠት ወደኋላ የማይል ይሆናል፡፡ እንዲህ ያለውን ዜጋ ለማፍራት ደግሞ የማኅበረሰብን ጤና መጠበቅ፤ ግንዛቤውንም በማስፋት ወደኋላ ከሚያስቀር የትኛውም የጤና እክል መታደግ የግድ ይላል፡፡ የተሻለን ነገ ለመፍጠር በሙሉ አቅሙ መንቀሳቀስ፣ ለማኅበረሰብ ችግሮችም መፍትሔ መሻት የሚቻለው ጤናው የተጠበቀ ዜጋ ነውና!
ዛሬም፣ አዳዲስ በኤች አይ ቪ የሚያዙ ሰዎች መኖራቸውና ስርጭቱንም መቆጣጠር አለመቻላችን እንደሀገር ትልቅ ኪሳራ የሚያስከትልብን መሆኑን የሚናገሩት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግና አስተዳደር ትምህርቶች መምህርትና የተማሪዎች ማበልጸጊያ ማዕከል ኃላፊ፣ ወ/ሪት ሊያ መሐሪ፣ ቫይረሱ በትውልድና በሀገር ላይ የተጋረጠ አደጋ ስለመሆኑ እያንዳንዱ ሰው ሊረዳውና ቀደም ባሉ ጊዜያት ሲሠራ የነበረው ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ በአዲስ መልክ ተጠናክሮ ሊከናወን እንደሚገባ ያሳስባሉ፡፡
ከጥቂት ጊዜያት በፊት፣ የሁለተኛ ደረጃ የግል ትምህርት ቤቶች ላይ ጥናት ያካሄዱት መምህርት ሊያ፣ በወቅቱ ስለ ኤች አይ ቪ ኤድስ ብንነጋገር የሚል ጥያቄ ካቀረቡላቸው ተማሪዎች መካከል አንዲት ተማሪ “ኤች አይ ቪ ኤድስ ጠፍቷል አይደል እንዴ” የሚል ምላሽ እንደሰጠች ያወሳሉ፤ የሌሎች ተማሪዎች ግንዛቤም ከእርሷ ብዙም የተለየ እንዳልነበረ ይናገራሉ፡፡ መምህርቷ እንዳሉት፣ ይህ የተማሪዎቹ ምላሽ ቫይረሱን አስመልክቶ ማኅበረሰቡ ያለው የግንዛቤ ደረጃ ምን ያህል አናሳ እየሆነ እንደመጣ ያመላክታል፤ የስርጭቱ መጠን መጨመርም ሌላው ምስክር ነው፡፡ እኛ ተማሪ በነበርንበት ጊዜ በየቦታው፣ በልዩ ልዩ መንገድ ስለ ኤች አይ ቪ የሚያስጠነቀቁ መልዕክቶች ይተላለፉ ነበር ያሉት መምህርት ሊያ፣ ከዚሁ ጋር አያይዘው፣ በተሠራው ጠንካራ የግንዛቤ ሥራ አብዛኛው ህብረተሰብ ቫይረሱን በተመለከተ የነቃ አመለካከት እንዲኖረው አድርጎ እንደነበርም ያስታውሳሉ፡፡ እርሳቸው እንዳሉት፣ አሁን አሁን ግን ግንዛቤን ለማስፋት የሚደረገው እንቅስቃሴም ሆነ ኅብረተሰቡ ለቫይረሱ ያለው ግንዛቤ ቀደም ሲል እንደነበረው አይደለም፡፡ ቫይረሱ እንደጠፋ አድርጎ ማሰብ፣ የእድሜ ማራዘሚያ መድሃኒትን እንደ መጨረሻ አማራጭ ሳይሆን፣ ልክ እንደ ቀላል መፍትሔ አድርጎ መውሰድና የሚያስከትለውን ጉዳት በጥልቀት አለመረዳት በኅብረተሰባችን መካከል ሰፍነው ከሚታዩ የተዛቡ አመለካከቶች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
የጤና ማዕከላት የሚያወጡት መረጃም እንደሚጠቁመው፣ የኤች አይ ቪ ምርመራ የሚያደርገው ሰው ቁጥርና የኮንዶም ሽያጭና ስርጭት መቀነስ፣ ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ የተለያዩ የወሊድ መቆጣጠሪያ መድሃኒቶች ሽያጭ መጨመር፣ ሰው ከኤች አይ ቪ ይልቅ እየፈራ ያለው ያልተፈለገ እርግዝናን መሆኑን ያሳያል፡፡ ኮንዶምን በአግባቡ በመጠቀም ቫይረሱንም ሆነ ያልተፈለገ እርግዝናን በአንድ ጊዜ መከላከል እየተቻለ የዚህን ያህል መዘናጋት መፈጠሩ ደግሞ በእጅጉ አስደንጋጭ፣ የማንቃቱንም ሥራ የሚያከብድ ነው፡፡ የቫይረሱ ስርጭትም ከትላንት የሚልቅ ወኔና ትጋትን የሚጠይቅበት ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ ስለሆነም ሥራው የቱንም ያህል ቢከብድም የግድ ሊሠራ፤ የማኅበረሰብ ንቃት ሊጨምር ይገባል፡፡ ይህ ካልሆነ፣ በዛኛው ትውልድ ካጣነው ሰው በላይ በዚህኛው ትውልድ ልናጣ እንችላለን፤ ይሄ ደግሞ ከግለሰብና ከቤተሰብ ባሻገር እንደ ሀገር የሚያስከትለው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ከባድ ነው፡፡
መምህርቷ እንዳሉት፣ በቀደሙ ጊዜያት በርካታ የግንዛቤ ሥራ ሲሠራ የነበረው በወቅቱ በነበሩ ጥቂት መገናኛ ብዙኃን ነበር፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ የመገናኛ ብዙኃን ቁጥር ጨምሯል፤ በርካታ የአየር ሰዓታትም አሏቸው፡፡ ትልቅ የማኅበረሰብ ችግር የሆነውን ኤች አይ ቪ ግን ጉዳይ አድርገው ሲያነሱ አይስተዋሉም፡፡ መገናኛ ብዙኃን ከፍተኛ ማኅበራዊ ኃላፊነት ያለባቸው እንደመሆናቸው መጠን እንዲህ ያሉ ጉዳዮችን አካተው እንዲሠሩ ግዴታ ሊጣልባቸው ይገባል፡፡
በቫይረሱ የሚያዘው ሰው ቁጥር ሲጨምር ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዘው ወጣቱ ነው ያሉት መምህር ሊያ፣ ወጣቱን በሚገባ ማስተማርና መለወጥ ካልቻልን ነገ ችግሩ የእያንዳንዳችንን በር ማንኳኳቱ፤ የራሳችን የሆነው ሰው ላይ መጋረጡ አይቀርም፤ ስለሆነም መፍትሔውን ከመንግሥት ብቻ ከመጠበቅ ይልቅ፣ ከመገናኛ ብዙኃን በተጨማሪ ሁሉም አካል የኤች አይ ቪን ጉዳይ በባለቤትነት መመልከት፣ በየትምህርት ተቋማቱ ያሉ፤ በተለይም በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚገኙ መምህራን ባገኙት አጋጣሙ ሁሉ ከሚሰጡት መደበኛ ትምህርት ጎን ለጎን ቫይረሱን የተመለከቱ መልዕክቶችን ለተማሪዎቻቸው ማስተላለፍ አሊያም፣ ትክክለኛ መረጃ የሚያገኙባቸውን ቦታዎችና መንገዶች መጠቆም መቻል ይኖርባቸዋል፡፡
እንደ ማኅበረሰብም በየድረገጹና በተለያዩ አጋጣሚዎች የምናወራቸውን ነገሮች ተወት አድርገን ትውልድን ለሚሰራ፤ ከጥፋት ለሚታደግ ጉዳይ ጊዜና ትኩረት ልንሰጥ እንደሚገባ አጽንዖት የሚሰጡት መምህርቷ፣ ከዚሁ ጋር አያይዘው በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በደላሎች የሚሠራው ሥራ እጅግ አስደንጋጭ መሆኑን አንሰተው፤ ሴተኛ አዳሪነት ሕግን የጣሰ ተግባር በሆነባት ሀገራችን ታዳጊ ሕጻናትን ለወሲብ ንግድ ማመቻቸት እየተስፋፋ የሚዘልቅ ከሆነ ችግሩ የባሰ እየከፋ የሚሄድ መሆኑን ያሳስባሉ፡፡ ስለሆነም ኅብረተሰቡ እንዲህ ያለውን የማኅበረሰብን እሴት ሸርሽሮ የሚጠፋ፣ የትውልድና የሀገር ዕድገት ዕንቅፋት የሆነ ጉዳይ ችላ ብሎ ጊዜውን በሌሎች ጉዳዮች ሊያጠፋ አይገባም በሚለው አስተያየታቸው ላይ አስምረውበታል፡፡
አንዳንድ ሴት ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ለትምህርትና የንጽህና መሣሪያ ያሉ ወጪዎቻቸውን ለመሸፈን የሚያስችላቸውን ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ ለኤች አይ ቪና ተያያዥ በሽታዎች በሚያጋልጣቸው ሁኔታዎች ውስጥ እንደሚገቡ የጠቁሙት መምህርቷ፣ ይህንን የሴት ተማሪዎችን ችግር ለመቅረፍና በዕውቀት የበለጸጉና ጤናማ ዜጋ ሆነው እንዲወጡ ለማስቻል በተለያዩ ክበባት አማካኝነት ገቢ ማስገኛ እንቅስቃሴ በማካሄድና በማገዝ ወደ ማይፈልጉት ሕይወት እንዳይገቡ መጠበቅ፣ ብሎም ለቫይረሱ የሚኖራቸውን ተጋላጭነት መቀነስ ይቻላል ይላሉ፤ ከዚህ በተጨማሪ ሁሉም ተማሪ ትምህርቱን እየተከታተለ ጤናማ በሆነ መንገድ ገንዘብ የሚያገኝበት ሁኔታ ትምህርቱ በሚከታተልበት አካባቢ ቢመቻችለት አሊያም፣ ከትምህርት ውጪ ያለውን ጊዜ በአላስፈላጊ ቦታዎች እንዳያሳልፍ በፈቃደኝነት አገልግሎት እንዲሰጥ የሚያስችሉ ሁኔታዎች ቢመቻቹለት ወጣቱን ለቫይረሱ የሚኖረውን ተጋላጭነት በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ ይቻላል የሚል መልእክትም አስተላልፈዋል፡፡

Alarm: