የዶ/ር ጽጌረዳ የኤድስ ቀን ላይ ያደረጉት ንግግር/መልዕክት/

የተከበሩ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ የተከበሩ ክብርት ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ፣ የተከበሩ ክብርት ዶ/ር ሊያ ታደሰ የጤና ሚ/ር ሚንስትር፣ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮች፣ የተከበራችሁ ማህበራትና ጥምረቶች፣ የባለድርሻ አካላትና የአጋር ድርጅቶች ከፍተኛ አመራሮች፣ የለሚ ኢንደስትሪያል ፓርክ ስራ አመራሮች እና ሰራተኞች፤ እንዲሁም የዚህ በዓል ታዳሚዎች ክቡራትና ክቡራን፣ ከሁሉ አስቀድሜ በሀገራችን “ኤችአይቪን ለመግታት፤ ዓለምአቀፋዊ ትብብር ፣ የጋራ ኃላፊነት” በሚል መሪ ቃል ለ33ኛ ጊዜ ታሰቦ ለሚውለው የአለም ኤድስ ቀን እንኳን አደረሳችሁ በማለት በፌደራል ኤችአይቪ/ኤድስ መከ/መቆ/ጽ/ቤት እና በራሴ ስም ለማቅረብ እወዳለሁ ፡፡
ኤች አይቪ ኤድስ በሀገራችን በተከሰተባቸው በመጀመሪያዎቹ ሁለት አስርት አመታት ውስጥ፣ በየዓመቱ በብዙ ሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎቻችን የሞት ምክንያት በመሆን፣ አረጋውያንን ያለ ጧሪ፣ ህፃናትን ያለ አሳዳጊ በማስቀረት፣ ማህበረሰባችንን ለከባድ ማህበራዊ፣ ስነ ልቦናዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ውስጥ የጨመረ፣ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡
ከዚህ ሀገራዊ ቀውስ ለመውጣት በየደረጃው ያለው የፖለቲካ አመራሩና ምክር ቤቶች፣ ልዩ ልዩ የሙያ ማህበራትና አደረጃጀቶች፣ ማህበራትና ጥምረቶች፣ አጋር ድርጅቶችና ባለድርሻ አካላት፣ በቁርጠኝነትና በባለቤትነት ሚናቸውን በመወጣታቸውና ተጨባጭ እርምጃዎችን በመውሰዳቸው፣ የቫይረሱን ስርጭት በመግታትና የሞት ምጣኔን በመቀነስ ረገድ፣ ብዙዎቹን የዓለም ሀገሮች ያስደመመ ፈጣንና ስኬታማ ውጤቶችን አስመዝግበናል፡፡ ይሁን እንጂ በሂደቱና በነበረው ሁለንተናዊ ትብብርና የጋራ ሀላፊነት፣ በተገኘው ትልቅ ሀገራዊ ድል በመርካትና በመዘናጋታችን፣ ኤችአይቪ በተለይ የልማታችን ምንጭ የሆነውን ወጣቱንና አምራቹን ኃይል፣ እንዲሁም ይበልጥ ተጋላጭ የሆነውን የማህበረሰብ ክፍል እየጐዳ መሆኑን ሀገራዊ የኤችአይቪ ስርጭት ሁኔታ መረጃ ያሳያል፡፡ ከማሳያዎቹ አንዱ ላለፉት አሰርት ዓመታት አዲስ በኤችአይቪ የመያዝ ምጣኔ ባለበት እየረገጠ በሚፈለገው ደረጃ ማውረድ አለመቻሉ ነው፡፡ ይህም ከ2010 እ.ኤ.አ ከነበረበት ምጣኔ በ75 ከመቶ መቀነስ ሲገባ በ2019 እ.ኤ.አ ያለው መረጃ የሚያሳየው በ52 ከመቶ ብቻ መቀነስ መቻሉን ነው፡፡
የአገራችን የኤችአይቪ የስርጭት ምጣኔ 0.93% ሲሆን በዚህም ስሌት 669,236 በላይ የሚሆኑ ወገኖች ኤችአይቪ በደማቸው እንደሚገኝ የ2019 አገራዊ የኤችአይቪ ስርጭት ግምት (HIV estimates and projection spectrum) ያሳያል፡፡ በዚህ መረጃ መሰረት፣ በሀገራችን 14,843 ሰዎች፣ በየዓመቱ አዲስ በኤችአይቪ የተያዙ ሲሆን፣ 67% የሚሆነው ዕድሜያቸው ከ30 ዓመት በታች የሚገኙ አምራችና የነገ የሀገር ተረካቢ የሆኑ ወጣቶችና ህጻናት ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ 20% አዳዲስ የተያዙ ሰዎች ዕድሜያቸው ከ20-24 ዓመት የሚሆኑ ወጣቶችና 19% የሚሆኑት ደግሞ ከ0-4 ዓመት የሚገኙ ህጻናት ናቸው፡፡ ይህ የሚያሳየው ዛሬም የኤችአይቪ ስርጭት ሁኔታ አሳሳቢና ከችግሩ ለመላቀቅ እስከዛሬ ከተሰራው የበለጠ ሁሉን አቀፍ ትብብርና የጋራ ሀላፊነትን የሚጠይቅ፣ ልዩ ትኩረት በተለይም ለወጣቶችና ህጻናት እንዲሁም ሌሎች ተጋላጭ ህብረተሰብ ክፍሎች፣ የላቀ ቁርጠኝነትና ተነሳሽነት የሚያስፈልገው፣ በከፍተኛ ትጋትና ጥንቃቄ፣ ሌት ከቀን የሚያባትል ስራ የሚጠብቀን መሆኑን ነው፡፡
በሌላ በኩል ምንም እንኳን ከ500 ሺህ በላይ የሚሆኑ ኤች አይቪ በደማቸው የሚገኝ ወገኖቻችን የጸረ ኤች አይቪ መድሃኒት ቢውስዱም፣ በአጠቃቀም ሂደት የሚታዩ ችግሮች ማለትም መድኃኒት የማቋረጥ፣ ሽፋኑ በሚፈለገው ደረጃ አለመድረስ መኖራቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ከውጭ ሀገር ለጋሃሽ ድርጅቶች በብዙ ድካም በተገኘ ገንዘብ፣ በውጭ ምንዛሬ እየተገዛ፣ የሚመጣውን የጸረ ኤች አይቪ መድሃኒት፣ በትክክልና በሀኪም ትዕዛዝ ብቻ ካለተወሰደ የዜጎቻችንን ህይወት ከሞት አይታደግም፤ ጤናማና ምርታማ ሆነው ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት አስተዋጽኦ አያበረክቱም፡፡ የቫይረሱን ስርጭት በመግታት ረገድም ሃላፊነታቸውን አይወጡም፡፡ ከተመሰቃቀለ የጤና ችግር በመውጣትም ሰላማዊ ኑሮ መኖር አይችሉም፡፡
በመሆኑም በመድሀኒት አጠቃቀም ረገድ የሚታዩ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ለመፍታት፣ ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝ ወገኖች፣ ኤች አይቪ በደማቸው የሚገኝ ማህበራትና ጥምረቶች፣ የጤና ባለሙያዎችና ኬዝ ማናጀሮች፣ የሐይማኖት አባቶች እንዲሁም የእነዚህን ወገኖቻችንን ግንዛቤ በማሳደግ ረገድ ድርሻ ያላችሁ ወገኖች፣ በሀገራዊ ትብብርና በላቀ ሀላፊነት በመስራት ተጨባጭ ውጤት እንድታዝመዘግቡ በዚሁ አጋጣሚ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡
በተጨማሪም የልማትና የኢንዱስትሪ ተቋማት በርካታ ወጣቶችና አምራች ኃይሉን የያዙ ሲሆኑ እነዚህ ሠራተኞች በአብዛኛው ከቤተሰቦቻችው ወይም ከትዳር አጋሮቻቸው ተለይተው ረዘም ያለ ጊዜ የሚያሳልፉ በመሆናቸው ለኤችአይቪ ተጋላጭ ባህሪያት ይስተዋልባቸዋል፡፡ በተቃራኒው የተሟላ የኤችአይቪ የማስተማር፣ የህክምናና ክብካቤ ሥራዎችን በጋራ በማቀድ ተግባራዊ በማድረግና ለሚመለከታቸው አካላት በማሳወቅ ረገድ ሰፊ ክፍተቶች እንዳሉ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ስለሆነም በዚህ ዓለም አቀፍ የኤድስ ቀን ይህ ቦታ ሲመረጥ ዕለቱን አስቦ ለመዋል ብቻ ሳይሆን ዘርፉን ከሚመሩ አካላት ጋር በመወያየት ዘለቀታ ያለው መፍትሔ በመስጠት ሠራተኛው ተደራሽ የሚሆንበትና ራሱን ከኤችአይቪ የሚከላከልበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ጭምር ነው፡፡
የተከበሩ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣የተከበሩ ክብርት ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ፣ የተከበሩ ክብርት ዶ/ር ሊያ ታደሰ የጤና ሚ/ር ሚንስትር፣ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮች፣ የተከበራችሁ ማህበራትና ጥምረቶች፣ የባለድርሻ አካላትና የአጋር ድርጅቶች ከፍተኛ አመራሮች፣ የለሚ ኢንደስትሪያል ፓርክ ስራ አመራሮች እና ሰራተኞች፤ እንዲሁም የዚህ በዓል ታዳሚዎች ክቡራትና ክቡራን፣
ወቅቱ የኮሮና ቫይረስ ወረሽኝ የተከሰተበት በመሆኑ ወረርሽኙን ለማቆም የሚደረገው ርብርብ የሁሉንም አካላት ትኩረት ይፈልግ ስለነበር የኤችአይቪ መከላከል ስራዎች መቀዛቀዝ ታይቶባቸው እንደነበር ተስተውሏል፡፡ በአንጻሩ የተባበሩት መንግስታት የኤድስ ፕሮግራም (UNAIDS) ወቅታዊ መግለጫ እንደሚያሳየው ጥምር የሆነው የኤችአይቪና የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሊገታ የሚችለው ወቅታዊ መረጃዎችንና የባህሪ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ መልዕክቶችን ለተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች በተለይም ይበልጥ ተጋላጭ ለሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች በተከታታይ ተደራሽ በሆነ መልኩ ማስተላለፍ ሲቻል መሆኑን ያስረዳል፡፡
ኤችአይቪ/ኤድስ የማህበረሰብ ጤና ችግር እንዳይሆን መስራት፣ ኤችአይቪ/ኤድስን በመከላከል ረገድ የተፈጠረው መዘናጋትና ቸልተኝነት ለመስበር፣ ይሄን ተከትሎ የተከሰተው በኤድስና ተያያዥ በሽታዎች የመሞትና በአዲስ የመያዝ ምጣኔ ለመቀነሰ፣ ማህበረሰባችን ኤች አይቪን ለመከላከል የሚያስችለው ግንዛቤ እንዲያጎለብት የሚያስችሉ ፕሮግራሞችን በመንደፍ ለመስራት ከኤች አይቪ ነጻ፣ ጤናማና አምራች ትውልድ ለመፍጠር ወቅቱን የሚመጥኑ ስልቶችን ተግባራዊ ለማድረግ በጋራ መረባረብ አማራጭ የማይቀመጥለትና ለነገ የማንለው ሀገራዊ ሀላፊነታችን መሆኑን ተገንዝበን ላስቀመጥነው ራዕይ መሳካት እንድንረባረብ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡ በመጨረሻም ይህ የዓለም ኤድስ ቀን የተሳካ ይሆን ዘንድ አስተዋጽዖ ላደረጉ አካላት ሁሉ በፌደራል ኤችአይቪ/ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽ/ቤት ስም ላቅ ያለ ምስጋናዬን አቀርባለሁ፡፡
“ኤችአይቪን ለመግታት፤ ዓለምአቀፋዊ ትብብር ፣ የጋራ ኃላፊነት!” አመሰግናለሁ!

የዶ/ር ጽጌረዳ ንግግር/መልዕክት/

Alarm: