የዶ/ር ጽጌረዳ ንግግር/መልዕክት/

የተከበሩ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ የተከበሩ የአፋር ብሄርዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ፣ የተከበራችሁ የፌደራልና የአፋር ክልል ከፍተኛ አመራሮች፣ የተከበራችሁ የአጋር ድርጅቶችና ባለድርሻ አካላት ከፍተኛ አመራሮች፣የዚህ በዓል ታዳሚዎች ክቡራትና ክቡራን፣ ከሁሉ አስቀድሜ በሀገራችን ‹‹ማህበረሰብ የለውጥ አቅምነው! ፡፡›› በሚል መሪ ቃል ለ32ኛ ጊዜ ለመናከብረው የአለም ኤድስ ቀን እንኳን አደረሳችሁ፡፡
ኤችአይቪ/ኤድስ በዓለማችን መከሰቱ ከታወቀበት እኤአ ከ1981 ጀምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ32 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ያጡ ሲሆን 37.9 ሚሊዮን ሰዎች ደግሞ በአሁኑ ጊዜ ኤችአይቪ በደማቸው እንደሚገኝ ይገመታል፡፡ በየዓመቱም ከ1.7 ሚሊዮን የሚሆኑ አዲስ በኤችአይቪ የሚያዙ ሰዎች እንዳሉና 1.1 ሚሊዮን ሰዎች ለህልፈት እንደሚዳረጉ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ የአገራችን የኤችአይቪ የስርጭት ምጣኔ 0.91% ሲሆን በዚህም ስሌት 649,000በላይ የሚሆኑ ወገኖች ኤችአይቪ በደማቸው እንደሚገኝ የ2019 አገራዊ የኤችአይቪ ስርጭት ግምት (HIV estimates and projection spectrum) ያሳያል፡፡ ሆኖም የስርጭቱ ምጣኔ ከክልል ክልል፣ በክልል ውስጥ ከአንድ ቦታ ሌላ ቦታ፣ በተለያዩ ማህበረሰብ ክፍሎች እንዲሁም በከተማና በገጠር በከፍተኛ ደረጃ የሚለያይና በአንዳንድ ቦታዎች ስርጭቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ የኤችአይቪ ስርጭት ከፍተኛ ከነበረበት አሁን ወዳለበት 0.91% ለመቀነስ ማህበረሰቡ ያበረከተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ሲሆን የዘንድሮም የአለም ኤድስ ቀን የሚከበረው የማህበረሰብን ሚና ለማጉላት ነው፡፡
እንደ ሀገር የተገኘውን ድል ተከትሎ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተፈጠረውን ሰፊ መዘናጋትና ቸልተኝነትን ለመቅረፍ በተለይም ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎችን ተኮር የሆነ የመከላከል ስራ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ ማህበረሰቡ በማህበራዊ ትስስር የኤችአይቪ ምርመራ ስልት /Social Networking Strategy/፣ ከፍተኛ አተዋጽዖ እንዲያደርግ እና በማህበረሰብ አቀፍ ድጋፍና እንክብካቤ ስራዎች፣ በማህበረሰቡ ውስጥ የሚገኙ የበጎ ፈቃድ የማህበረሰብ አገልግሎት ሰጭ ሰዎች ትርጉም ያለው ስራ እንዲያከናውኑ፣ የጸረ-ኤችአይቪ መድሀኒትን የሚወስዱ ሰዎች መድሀኒታቸውን እንዳያቋርጡና በአግባቡ ክትትል እንዲያደርጉ፣ ኤችአይቪ በደማቸው በሚገኝ በጎ ፈቃደኛ ወገኖች በስፋት እንዲሳተፉና የመሳሰሉ ስራዎች እንዲሰሩ ከማድረግ አንጻር እንደ ሀገር ረጅም ርቀት ለመሄድ ተሞክሯል፡፡

ይሁን እንጂ ዛሬም ቢሆን ያልተሻገርናቸው በርካታ ተግዳሮቶች በመኖራቸው ምክንያት፣ ተጠባቂው የባህሪ ለውጥ ባለመምጣቱ፣ በኤችአይቪ/ኤድስ በየአመቱ ለ11 ሺህ ዜጎቻችን ሞት ምክንያት እየሆነ ይገኛል፡፡ በተለይም በየደረጃው በሚገኘው ከፍተኛ አመራር፣ በልዩ ልዩ ባለድርሻ አካላትና የማህበረሰብ ክፍሎች እንዲሁም አጋር ድርጅቶች ተገቢውን ትኩረት እያጣ በመምጣቱ የማህበረሰብ ጤና ችግር ሆኖ ቀጥሏል፡፡
የተከበሩ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ የተከበሩ የአፋር ብሄርዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ፣ የተከበራችሁ የፌደራልና የአፋር ክልል ከፍተኛ አመራሮች፣ የተከበራችሁ የአጋር ድርጅቶችና ባለድርሻ አካላት ከፍተኛ አመራሮች፣የዚህ በዓል ታዳሚዎች ክቡራትና ክቡራን፣
ከሁለት አስርት አመት በፊት፣ በኤች አይቪ ኤድስ ምክንያት ተፈጥሮ የነበረው የህይወትና የኑሮ ምስቅልቅል፣ ተስፋ የመቁረጥና የሞት ድባብ የተሻገርንው፣ ዘመን ተሻጋሪና አኩሪ ተግባር በፈጸሙት፣ መገለልና መድሎውን ሰበረው በሚዲያው፣ በልዩልዩ የጎዳና ላይ ሁነቶች፣ በየአደባባዩና በየማህበራዊ ግንኙነቱ፣ ሌት ተቀን ሳይታክቱ በሰሩ፣ ዘመን የማይሽረው፣ ታሪክ የማይረሳው ድል ባለቤት በነበሩ የማህበረሰብ ክፍሎች ነው፡፡ ስለሆነም ማህበረሰቡ የለውጥ አቅም ነው ሲባል በምክንየት ነው፡፡ ማህበረሰቡ አቅም እንዲሆን ከከፍተኛ የመንግስት አመራሮች ጀምሮ በየደረጃው የሚገኙ ውሳኔ ሰጭዎች፣ ኤችአይቪ በደማቸው የሚገኝ ዜጎች ላይ የሚደርሰውን መገለልና መድሎ ለመቀነስ መስራት ይኖርባቸዋል፡፡ በዓርዐያነት በመምራቱ ሂደት፣ የፖለቲካ አመራሮች በማህበረሰቡ ውስጥ በመሳተፍና ለማህበረሰቡ አስተዋጿቸውን ማሳየት አለባቸው፡፡
ትርጉም ያለው የማህበረሰብ ተሳትፎ በተለይ ኤችአይቪ በደማቸው የሚገኝ ወገኞች በኤችአይቪ ፕሮግራሞች ዝግችትና ትግበራ ወቅት በበቂ ሁኔታ ባለቤት ሆነው እንዲሳተፉ ማድረግ፤ ማህበረሰቡ ችግሬ ነው ብሎ የለየውን ጉዳይ በቀላሉ ለመፍታት ያስችለዋል፡፡ ይህን ለማድረግ እነዚህ የማህበረሰብ ክፍሎች በውሳኔ ሰጭነት መሳተፍም ይገባቸዋል፡፡
በህጎችና በፖሊሲዎች ዙሪያ ማህበረሰቡ በግልጽ በመወያትና የተጋላጭ ማህበረሰብ ክፍሎች ድምጽ በመሆን ፖሊሲዎችና የህግ ማዕቀፎች ሲቀረጹ የኤችአጭቪ ተጋላጭነትን በሚቀንስ መልኩ እንዲዘጋጁ የሚያበረክቱትን አስተወጽኦ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ምቹ ሁኔታ መፈጠር ያስፈልጋል፡፡ በተለይ አፍላ ወጣቶችን ለኤችአይቪ የሚያጋልጡ ሁኔታዎች በህግ አግባብ ሊቀረፉ የሚችሉበት ሁኔታ ማመቻቸት ይገባል። አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ በማህበረሰብ-መር ተቋማት እና ኤችአይቪ በደማቸው በሚገኝ ሰዎች ማህበራትና ጥምረቶች የነበራቸው ሚና እየተቀዛቀዘና ፋይዳቸው እየቀነሰ በመምጣቱ እንደአዲስ ውይይት መጀመር አስፈላጊ ነው።
የአገልግሎት አቅርቦትና አጠቃቀም ላይ ከማህበረሰብ የሚገኘው መረጃ ተጨባጭና ትክክለኛ በመሆኑ፣ ሀገር አቀፍ የኤችአይቪ/ኤድስ ፕሮግራሞች ዝግጅትና ትግበራ እነዚህን መረጃዎች ማዕከል ያደረገ ሊሆን ይገባል፡፡ እንዲሁም አሰራሩ የብሄራዊ የኤችአይቪ/ኤድስ የመረጃ ስርአት አካል ሆኖ ጥቅም ላይ የሚውልበትን ሁኔታ ማመቻቸትና ለዕቅድ እንዲያገለግል ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ጥራቱን የጠበቀ የኤችአይቪ አገልግሎት በወቅቱ የማቅረብ ተጠያቂነትን ለማህበረሰብ በማድረግ ጥራት ያለው የጤናና የማህበራዊ አገልግሎት ተደራሽነትን ማረጋገጥ የሚያስችል አሰራር መዘርጋትም ይገባል፡፡
በአጠቃላይ በማህበረሰብ አቅም ኤችአይቪ/ኤድስ የማህበረሰብ ጤና ችግር እንዳይሆን መስራት፣ ኤችአይቪ/ኤድስን በመከላከል ረገድ የተፈጠረው መዘናጋትና ቸልተኝነት ለመስበር፣ ይሄን ተከትሎ የተከሰተው በኤድስና ተያያዥ በሽታዎች የመሞትና በአዲስ የመያዝ ምጣኔ ለመቀነሰ፣ የማህበረሰቡ ኤች አይቪን ለመከላከል የሚያስችለው ግንዛቤ ለማሳደግ፣ ወቅቱ የሚጠይቀው አብይ ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑም የሚመለከታችሁ ሁሉ ሀላፊነታችሁን፣ ዛሬም እንደ ትናንቱ በመወጣት፣ ከኤች አይቪ ነጻ፣ ጤናማና አምራች ትውልድ በመፍጠር፣ የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን እንድናደርግ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡
ማህበረሰብ የለውጥ አቅም ነው!
አመሰግናለሁ፡፡

አፋር ክልል/ 32ኛው የአለም ኤድስ ቀን አከባበር
ህዳር፣ 2012

Alarm: