የዶ/ር ሊያ ታደሰ የአለም የኤድስ ቀን ላይ ያደረጉት የመክፈቻ ንግግር

ክብርት የኢፌዴሪ ፕሬስደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ ክብርት ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ፣ የተከበሩ ዶ/ር ጽጌረዳ ክፍሌ ፌደራል ኤች አይቪ/ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር፣ የተከበራችሁ የባለድርሻ አካላትና የአጋር ድርጅቶች ከፍተኛ አመራሮች፣ ማህበራትና ጥምረቶች፣ ክቡራትና ክቡራን፣ በቅድሚያ በአለም አቀፍ ደረጃ፣ በዛሬው ዕለት ታሰቦ ለሚውለው የዓለም የኤድስ ቀን፣ በጤና ሚኒስቴርና በራሴ ስም እንኳን አድረሳችሁ ለማለት እወዳለሁ፡፡
ይህንን ዓለም አቀፍ በዓል ስናከብር፣ በዓለም ዙሪያ ያሉ ሰዎች፣ ኤችአይቪ በደማቸው ለሚገኝና በቫይረሱ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች፣ ድጋፋቸውን ለማሳየት፣ አብሮነታቸውን ለማረጋገጥ፣ ትብብራቸውን ለመግለጽ፣ እንዲሁም በኤድስና ተያያዥ በሽታዎች ህይወታቸውን ያጡትን ወገኖች በማስታወስ፣ ተጨማሪ ሞት፣ ተጨማሪ የስነልቦና ስብራት፣ ማህበራዊ ቀውስ፣ ኢኮኖሚያዊ ምስቅልቅል፣ እንዳይፈጠር የድርሻቸውንና ማህበራዊ ግዴታቸውን ለመወጣት ቃል የሚገቡበት መሆኑን በማሰብ ነው፡፡
የኤች አይቪ ስርጭትን የመግታት ጉዳይ በጤናው ዘርፍ ተቋማት ርብርብ ብቻ ውጤት የሚገኝበት አይደለም፡፡ የማይመለከተው የህብረተሰብ ክፍል፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆነ ተቋምና ድርጅት የለም፡፡ ለዚህም ነው፣ በዚህ ዓመት ‹‹ኤች አይቪን ለመግታት፣ ዓለም አቀፋዊ ትብብር፣ የጋራ ሃላፊነት›› በሚል መሪ ቃል በሀገራችን ቀኑን አሰበን የምንውለው፡፡
በሀገራችን ያለው የቫይረሱ ስርጭት ሁኔታ በአንጻራዊ በየዓመቱ እየቀነሰ መምጣቱን ልዩልዩ ጥናቶች የሚያመላክቱ ቢሆንም በተለይም ይበልጥ ተጋላጭ በሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ በአዲስ አበባ ከተማ፣ በጋምቤላ ክልል፣ በብዙዎቹ የሀገራችን ከተሞች፣ ወደ ከተማነት በማደግ ላይ በሚገኙ ትናንሽ መንደሮች፣ በኮንሰትራክሽን ስራዎች ላይ በተሰማሩ ወጣቶች፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ በግዙፍ የአበባ ልማት እርሻዎችና በመሳሰሉት በርከት ያሉ ሰዎች ተሰባስበው ቢሰማሩባቸው የስራ ዘርፍ አከባቢዎች፣ የቫይረሱ ስርጭት በሚፈለገው ልክ ሲቀንስ አይታይም፡፡
በዚያው ልክ ኤች.አይ.ቪ በደማቸው የሚገኝ ወገኖች፣ ቤተሰባቸውን የኤች.አይ.ቪ ምርመራ በማድረግ፣ የፀረ ኤች አይ ቪ ህክምና አገልግሎቶች ተጠቃሚዎች፣ ህክምናቸውን ሳያቋርጡ፣ መድሀኒታቸውን በአግባቡ በመውሰድ፣ ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ከቫይረሱ በመታደግ፣ ኤች አይቪ በደማቸው የሚገኝ ወገኖች ላይ የሚደርሰውን አድሎና ማግለል በማቆም እንዲሁም በኤች አይቪ ምክንያት ወላጆቻቸውን ያጡና ለችግር የተጋለጡ ህፃናትና አረጋዊያንን መደገፍና በመንከባከብ ማህበራዊ ኃላፊነታቸነን ከመወጣት አንጻር ያልተሸገርናቸው ችግሮች አሉ፡፡
ችግሩን በአግባቡ በመረዳትና የሚያስከትለውን ቀውስ በመገንዘብ፣ ችግሩን ሊፈታ በሚያስችል ደረጃ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎና ርብርብን፣ የከፍተኛ አመራሩን፣ የክልል የኤች አይቪ/ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ምክር ቤቶችን፣ በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት ተቋማትን፣ የኪነጥበብ ባለሙያዎችን፣ የሀይማኖት አባቶችና ተቋማትን፣ የሚዲያውን፣ የአጋር ድርጅቶችንና መሰል አደረጃጀቶችን ትኩረት አላገኘም፤ በጋራ ትብብር፣ በሀገራዊ ሀላፊነት፣ በጠንካራ ቁርጠኝነት፣ በሀገር ፍቅር ስሜት የተያዘ አጀንዳ አይደለም፡፡
ክብርት የኢፌዴሪ ፕሬስደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ ክብርት ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ፣ የተከበሩ ዶ/ር ጽጌረዳ ክፍሌ ፌደራል ኤች አይቪ/ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር፣ የተከበራችሁ የባለድርሻ አካላትና የአጋር ድርጅቶች ከፍተኛ አመራሮች፣ ማህበራትና ጥምረቶች፣ ክቡራትና ክቡራን፣
ሀገራችን ኢትዮጵያ ከድህነት ታላቃ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች ተርታ እንድትሰለፍ፣ ጤናው የተጠበቀ፣ በክህሎት፣ በዕውቀት፣ በአመለካከት የዳበረ፣ ምርታማና ውጤታማ አምራች ትውልድ ያስፈልጋታል፡፡ የሀገራችንን የወደፊት እጣ ፈንታ የመወሰንና ይህንን ትውልድ በሁሉም ዘርፍ የመገንባት፣ የማነጽ ሀላፊነት ድግሞ የእኛ ታሪካዊ ሃላፊነት ነው፡፡ ዛሬ በያለንበት የሀላፊነት እርከን፣ የሙያ ዘርፍ፣ ሃላፊነታችንን በተወጣንበት ልክ የሀገራችን የደፊት ዕጣ ፈንታ መወሰኑ አይቅርም፡፡
በመሆኑም ኤች አይቪ/ኤድስን ስርጭት የመግታት ጉዳይ፣ በሽታን ከመከላከል የላቀ ትርጉም ያለው መሆኑን መገንዘብ ይጠይቃል፡፡ የማህበራዊ ቀውስ፣ የስነልቦና ስብራት፣ የኢኮኖሚ ዕድገት ማነቆ፣ የሀገር ገጽታ ጥላሸት መሆኑን በመረዳት፣ ስርጭቱን ለመግታት፣ ሀገራዊ ትብብርና የጋራ ሃላፊነትን መውሰድ ይገባል፡፡

Alarm: