የዶ/ር ደረጀ ዱጉማ መልዕክት

የተከበሩ የሲዳማ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ደስታ ሌንዳሞ፣ የተከበሩ ወ/ሮ አበባ ዮሴፍ፣ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የሴቶችና ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ፣የተከበሩ ወ/ሮ ፊልሰን አብዱላሂ የሴቶች፣ህጻናት እና ወጣቶች ሚኒስቴር ሚኒስትር፣ የተከበሩ ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚንስትር፣ የተከበሩ ዶ/ር ጽጌረዳ ክፍሌ የፌደራል ኤች አይቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽ/ቤት ሀላፊ ፣ የተከበሩ አቶ ዮሐንስ ፣ የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ ሀላፊ ተወካይ፣ የፌደራልና የሲዳማ ክልል ከፍተኛ አመራሮች፣ የተከበራችሁ ማህበራትና ጥምረቶች፣ የባለድርሻ አካላትና የአጋር ድርጅቶች ከፍተኛ አመራሮች፣ የሐዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ስራ አመራሮች እና ሰራተኞች፤ እንዲሁም የዚህ በዓል ታዳሚዎች ክቡራትና ክቡራን፣ በቅድሚያ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ33ተኛ ጊዜ ለምናከብረው የዓለም የኤድስ ቀን እንኳን አደረሳችሁ ለማለት እወዳለሁ፡፡
በሀገራችን፣ አስቀድሞ በመከላከልና የአስተሳሰብ ለውጥ በማምጣት ላይ ትኩረት ያደረገ የጤና ፖሊሲን በመተግበር ባለፉት ጥቂት ዓመታት መሰረታዊ ጤና አገልግሎት በማስፋትና ተደራሽ በማደረግ፣ ህብረተሰቡ ጤናው የተጠበቀና ምርታማ እንዲሆን፣ በርካታ ስራዎች ተረሰርተዋል፡፡ የኤች አይቪ ኤድስ ስርጭትን በመግታት ረገደም በግለሰቦች ላይ ከሚፈጥረው ህመም ሞትና ስቃይ በተጨማሪ፣ በርካታና ውስብስብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የሚያስከትል መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት ልዩ ልዩ አደረጃጀቶችና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን፣ ልዩልዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ያካተተና በስፋት ያሳተፈ ሀገር አቀፍ አካል እንዲሁም ራሱን የቻለ መንግስታዊ አስፈጻሚ መስሪያ ቤት ማቋቋም በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡
የቫይረሱን ስርጭት የመግታቱ ስራ በቅንጅትና በህዝብ ተሳትፎ ላይ የተመሰረተ የመከላከልና የቁጥጥር ዘመቻ ተደርጎበት ስርጭቱ ካልተገታ በስተቀር፣ የሚያስከትለው የኢኮኖሚና የማህበራዊ ቀውስ እጅግ የሚያስፈራ መሆኑን በውል በመረዳት፣ የሚመለከታቸው ዓለም አቀፍና ሀገር አቀፍ ድርጅቶች፣ መንግስታዊ ተቋማትና ተጽዕኖ ፈጣሪ ታዋቂ ግለሰቦች፣ ልዩ ልዩ የሙያ እና የሲቪክ ማህበራትና የኤች አይቪ/ኤድስ ማህበራት ጥምረቶች እልህ አስጨራሽ ትግል አድርገዋል፡፡
በተለይም ኤች አይቪ ኤድስን ስርጭት በመግታት ረገድ አግባብ ያላቸው አካላት በሙሉ ለችግሩ ይበልጥ ትኩረት በመስጠት፣ የህብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግና የማበረሰብ ንቅናቄዎችን በስፋት በማካሄድ፣ ጤናማ አመለካከትና ባህሪ እንዲዳብር፣ የመከላከል ስራውን በተቀናጀ ሁኔታ በመስራትና ሴቶችና ህጻናትን ጨምሮ ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ራሳቸውን ከኤችአይቪ እንዲከላከሉ ማድረግና አስፈላጊውን ድጋፍና ክብካቤ እንዲያገኙ በማስቻል ረገድ በተደረገው ሰፊ ርብርብ፣ በርካታ ስኬቶች ተመዝግበዋል፡፡
ይሁን እንጂ በአሁኑ ሰዓት፣ በተገኘው ውጤት በመርካትና በመዘናጋታችን ምክንያት የሁሉም ባለድርሻ አካላትና አጋር ድርጅቶች ተሳትፎና ርብርብ መቀነሱን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ይሄንኑ ተከትሎ በተለይም ይበልጥ ተጋላጭ በሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች በአዲስ በቫይረሱ የመያዝና በኤድስና ተያያዥ በሽታዎች የመሞት ምጣኔው ከፍተኛ መሆኑን ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ በሁሉም መንግስታዊና መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት የኤች አይቪ/ኤድስን ጉዳይ በማካተት፣ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት በሚችልበት ደረጃ መስራት የሚገባቸው ቢሆንም በታሰበው ልክ በትኩረት ባለመሰራቱ ተጠባቂው ውጤት እየመጣ አይደለም፡፡ የክልል ኤች አይቪ/ኤድስ መከልከልና መቆጣጠር ምክር ቤቶች፣ በሁሉም ተቋም፣ ኤች አይቪ/ኤድስ ጉዳይ ተካቶ፣ ተገቢውን ትኩረት አግኝቶ፣ ተግባራዊ እንዲሆን በመከታተልና በመቆጣጠር ለመምራት ትልቅ ሀገራዊ ሀላፊነት ያለባቸው ቢሆንም እዚህ ግባ የሚባል ስራ እየሰሩ አይደለም፡፡
ኤችአይቪ/ኤድስ በየደረጃው ያለው አመራር አጀንዳ አለመሆኑ ችግሩን የበለጠ ውስብስብ ስላደረገው፣ እአአ በ2030 ኤድስ የማህበረሰባችን የጤና ችግር ወደማሆንበት ደረጃ ለማድረስ የተቀመጠውን ራዕይ እንዳናሳካ ትልቅ ተግዳሮት መሆኑ የማይቀር ነው፡፡
በመሆኑም ሀገርን መውደድ ከወንዝ ከተራራው፣ አጠቃላይ ያደግንበትን መንደርና አከባቢ ከመውደድ በዘለለ ሰውን መውደድ በመሆኑ፣ ባለን ውስን ሀብት ተክክለኛ፣ ደረጃውን የጠበቀና በህብረተሰቡ ተቀባይነት ያለው የኤች አይቪ ኤድስ መረጃ፣ ሁሉን አቀፍ መሰረታዊ የጤና አገልግሎት ለህብረተሰቡ ተደራሽ በማድረግ፣ ኤች አይቪ በደማቸው የሚገኝ ወገኖችንና በኤድስ ምክንያት ያለ አሳዳጊ የቀሩ ህጻናትን ተገቢ፣ ማህበረሰብ አቀፍ እንክብካቤ፣ ስነልቦናዊ ድጋፍ በመስጠት፣ ሴቶችን፣ ወጣቶችንና ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ራሳቸውን ከኤች አይቪ ለመከላከልና በራሳቸው የመከላከል እርምጃ ለመውሰድ አቅም እንዲኖራቸው በማስቻል ሰፊ ርብርብ ማድረግ ይገባናል፡፡
ከጎረቤት ሀገሮች፣ ከአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ድርጅቶች ጋር የኤች አይቪ ስርጭትን ለመግታት አስተዋጽዖ በሚያደርጉ እንቅስቃሴዎች ሁሉ በመተባበርና በመስራት እንዲሁም የኤች አይቪ ስርጭትን በመግታት ውስጥ በሀገር አቀፍ ደረጃ ራስን አቅም በማጎልበት፣ የውስጥና የውጭ ዕርዳታዎችን ለማሰባሰብና ለመጠቀም የሚያስችሉ አሰራሮችን በመዘርጋትና በአግባቡ በመተግበር በሀገራዊ ትብብር፣ በጋራ ሃላፊነትና በከፍተኛ ቁርጠኝነት መስራት ይገባል፡፡
የተከበራችሁ የሀዋሳና አከባቢዋ ነዋሪዎች፣ ክቡራትና ክቡራን
ሀገራችን ኢትዮጵያ በልጆቿ ታፍራና ተከብራ የኖረቸው፣ ሁሉም ትውልድ በየዘመኑ ሀገራዊ ሀላፊነቱን በመወጣት፣ ድልና ሀገራዊ አንድነትን እንዲሁም የሀገር ፍቅር ስሜትን ለቀጣዩ ትውልድ፣ በማስረከቡ ነው፡፡ ዛሬ የዚህን ቫይረስ ስርጭት በመግታት፣ ዜጎቻችንን ከሞት፣ ከህመምና ከስቃይ በመታደግ፣ ያለ አሳዳጊ የቀሩ ወጣቶችንና ህጻናትን በመንከባከብና በመደገፍ፣ ማህበረሰቡ በተለይም ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ ተፈላጊውን የባህሪ ለውጥ በማምጣት ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ከኤች አይቪ እንዲታደጉ በማድረግ ታሪካዊ ሀላፊነት አለብን፡፡ በሰራንው ልክ የታሪክ ተወቃሽ ወይም ተመስጋኝ መሆናችን የማይቀር የነገ ታሪካችን ነው፡፡
ስለሆነም የሲዳማ ክልል መስሪያ ቤቶች፣ በየደረጃው የምትገኙ የክልሉ ምክር ቤቶች አፈጉባኤዎች፣ የክልሉ መገናኛ ብዙሃን፣ የእምነት ተቋማትና መሪዎች፣ የሙያ ማህበራትና ታዋቂ ግለሰቦች፣ እንዲሁም መላው የሀገራችን ህዝቦች፣ የኤች አይቪ ስርጭትን በመግታት ረገድ፣ አሁን የተፈጠረውን መዘናጋትና ቸልተኝነት በመስበር፣ በከፍተኛ ሀገራዊ ትብብርና የጋራ ሀላፊነት ስሜት፣ ሰፊ ርብርብ እንድታደርጉ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡
‹‹ ኤች አይቪን ለመግታት ዓለም አቀፋዊ ትብብር፣ የጋራ ሃላፊነት!››
አመሰግናለሁ፡፡

Alarm: