የዶር ጽጌረዳ ንግግር

የተከበራችሁ፣ በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት የሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አመራርና አባላት፣ ዶ/ር ደረጄ ድጉማ የጤና ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ፣ የክልል የጤና ቢሮና የኤች አይቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽ/ቤት ኃላፊዎች፣ ኤችአይቪ በደማቸው የሚገኝ ማህበራት ጥምረቶች ኃላፊዎች፣ የሲቪክ ማህበራትና የአጋር ድርጅቶች አመራሮችና ባለሙያዎች፣ ክቡራትና ክቡራን፣ ከሁሉ አስቀድሜ ጥሪያችንን አክብራችሁ፣ የ2013 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት የስራ አፈጻጸም፣ አዳዲስ የኤችአይቪ ኢኒሼቲቮችና አዲሱን ስትራቴጂክ ዕቅድ ማስተዋወቂያ መድረክ ላይ፣ ታሪካዊቷና ጥንታዊቷ ውብ ሀገር፣ ቀደምት ከተማ፣ ደብረ ብርሀን፣ እንኳን ደህና መጣችሁ ለማለት እወዳለሁ፡፡
የፌዴራል ኤች አይቪ/ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽ/ቤት፣ የኤች አይቪ ስርጭትን ለመግታት፣ የተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ልዩልዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ያካተተና በስፋት የሚያሳትፍ ሀገር በቀል አካል እንዲኖረውና ራሱን የቻለ መንግስታዊ አስፈጻሚ መስሪያ ቤት ሆኖ በአዋጅ ቁጥር 276/1994 ሲቋቋም፣ የሀገሪቱን የኤች አይቪ ኤድስ ፖሊሲን አፈጻጸም ለመከታተልና ለመምራት ነው፡፡ በመሆኑም ኤች አይቪ/ኤድስን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚንቀሳቀሱ የፌደራልና የክልል መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን እንቅስቃሴ በማስተባበር፣ የስራ ቅንጅት እንዲኖር ሁኔታዎችን በማመቻቸት፣ ሌሎች ተዛማጅ ስራዎችን በመስራት፣ የኤች አይቪ ስርጭትንና የሞትን ምጣኔ በመቀነስ፣ መድሎና መገለልን በማስቀረት፣ እንደ ሀገር ተጨባጭ ውጤቶችን ማስመዝገብ የሚጠበቅበት መንግስታዊ ተቋም ነው፡፡
በዚሁ መሰረት ይህንን ሀገራዊ ጉዳይ የሚያሳካ፣ በየአምስት አመቱ ስትራቴጂክ ዕቅድ በማዘጋጀት፣ አፈጻጸም መርህ በማበጀት፣ በየግማሽ አመቱ ስራዎችን ከሚመለከታቸው አጋር ድርጅቶች፣ ባለድርሻ አካላትና ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመገምገም፣ የቀጣይ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ፣ ተጨበጭና በረካታ ስኬቶችን ማስመዝገብ ተችሏል፡፡ ኤች አይቪ/ኤድስ እንደሀገር በህብረተሰቡ ላይ አጥልቶ የነበረውን የሞት ድባብ፣ ህመምና ስቃይ፣ መገለልና መድሎ፣ በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ ተችሏል፡፡
ምንም እንኳን በዚህ መልክ ስኬቶች የተመዘገቡ ቢሆንም፣ በተገኘው ስኬት በመርካት፣ አሁናዊ ሁኔታውን በሚገባ ባለመረዳትና በመዘናጋት፣ ኤች አይቪ/ኤድስ ዛሬም በየዓመቱ ለአስር ሺዎች ሞት ምክንያት እየሆነ መሆኑ እያስተዋልን አይደለም፡፡ አሁንም እንደ ትናንቱ ወጣቱና አምራች የሆነው ሀይል በአዲስ በኤች አይቪ እየተያዘ መሆኑን እየተገነዘብን አይደለም፡፡ ያለፈውን የእስትራቴጂክ ዘመን ብንመለከት፣ በብዙዎቹ ክልሎች ተመሳሳይ ወይም ተቀራራቢ አፈጻጸምና ተጠባቂውን ውጤት አልተመዘገበም፡፡ ይበልጥ ተጋላጭ በሆኑት የህብረተሰብ ክፍሎችና በከተሞች፣ እንደ አዲስ አበባ፣ ድሬደዋና ሀረር እንዲሁም በጋምቤላ ባሉ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የስርጭት ምጣኔው ከሁለት በመቶ በላይ ነው፡፡ የስርጭት ምጣኔው አስጊና ልዩ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ቢሆንም የከፍተኛ አመራሩም ሆነ የሌሎች ባለድርሻ አካላት ትኩረትን አሁንም በሚፈለገው ልክ ሊያገኝ አልቻለም፡፡
ክቡራትና ክቡራን
አንድ ሀገር፣ በኢኮኖሚው፣ በማህበራዊና በፖለቲካው ዘርፍ ስኬታማ ለመሆን ጤናማና አምራች የሆነ የህብረተሰብ ክፍል ሊኖረው የሚገባ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ የጤናው ዘርፍ ስኬት፣ ፈርጀ ብዙ የሚሆነውም በዚሁ ምክንያት ነው፡፡ በጤናው ዘርፍ ያልተሳካላቸው ሀገሮች፣ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን፣ ማህበራዊ ፍትህን፣ የዳበረ ዴሞክራሲን ያረጋግጣሉ ተብሎም አይወሰድም፡፡ ኤች አይቪ/ኤድስ የሚያስከትለው ቀውስ ደግሞ ከጤና ችግርነቱ ባሻገር፣ ስነ ልቦናዊ ስብራት ጭምር ነው፡፡
በመሆኑም አሁን ካለንበት አዙሪት ውስጥ ለመውጣት፣ የቀጣዩን አምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ በተሟላ መንገድ መገንዘብና መተግበር ይጠይቃል፡፡ እስትራቴጂክ ዕቅዱ እ.ኤ.አ በ2025 ያስቀመጥናቸውን አንኳር ግቦችና በ2030 የያዝነውን ራዕይ ለማሳካት የሚረዱ ዋና ዋና የአፈጻጸም አቅጣጫዎችን የያዘ፣ የባለድርሻ አካላትና፣ የአጋር ድርጅቶችን፣ የከፍተኛ አመራሩንና ባለሙያውን የተቀናጀ አሰራር፣ ጠንካራ ቁርጠኝነትን፣ የነቃ ተሳትፎና ሀገርን ከኤች አይቪ ኤድስ ስርጭት ለመታደግ፣ የላቀ ተነሳሽነትን የሚጠይቅ ነው፡፡
የስርጭት ምጣኔው ከፍተኛ የሆነበትን አከባቢና ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ ማህበረሰቦችን በመለየትና እንደየአከባቢው ተጨባጭ ሁኔታ፣ ህብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ፣ ፍትሐዊ አገልግሎትን ተደራሽ በማድረግ፣ ባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ ከመቼውም በላይ በማስፋት፣ በእስትራቴጂክ ዕቅዱ የተያዙትን ግቦችና አበይት ዓላማዎች ለማሳካት ሰፊ ጥረት ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ በተለይም በሴቶች ላይ ያለው የቫይረሱ ስርጭት፣ ከስነ-ህይወታዊው ምክንያት በተጨማሪ በኢኮኖሚ የበላይነት፣ በጎጂ ባህላዊ ልማዶች ተጽኖዎችና የኑሮ ጉስቁልናና ተያያዥ ምክንያቶች፣ ከፍተኛ በመሆኑ፣ በልዩ ትኩረት፣ በላቀ ቁርጠኝነት መስራትን ይጠይቃል፡፡
ስትራቴጂክ ዕቅዱ ትግበራ ዕውን ለማድረግ ይበልጥ ትኩረት የሚፈልጉ የህብረተሰብ ክፍሎችን በመለየት፣ ስርጭቱ ከፍ ያለባቸውን ወረዳዎች ላይ የተለየ ትኩረት በመስጠት፣ ከአጋሮች ጋር ሆነን ስንጠቀምባቸው የነበሩ አዋጪ የሆኑ የአገልግሎት አሰጣጥ መንገዶችን ወጪ ቆጣቢና ቀጣይነትን በሚያረጋግጥ መልክ መተግበርን ይጠይቃል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ለተግባራዊነቱ እንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ ተግዳሮቶችን ከወዲሁ መፍታት ይገባል፡፡
በሌላ በኩል፣ ያለንበት ወቅት፣ አዲሱ የግሎባል ፈንድ የሚጀምርበት በመሆኑ፣ ተጨባጭ ለውጥ በሚያመጡ ዋና ዋና ጉዳዩች ላይ በማተኮር፣ በከፍተኛ ዲሲፕሊን በመምራትና በመገምገም ሀገራዊና ታሪካዊ ሀላፊነታችንን መወጣት ይገባናል፡፡ በመጨረሻም ይህንን ውይይት መድረክ በማዘጋጀት ድርሻ የነበራችሁን አካላት በሙሉ እያመሰገንኩ፣ የተከበሩ ዶር ደረጄ ዱጉማ፣ የጤና ሚኒስትር ሚኒስቴር ዴኤታ፣ የውይይት መድረኩን እንዲከፍቱልን፣ በማክበር እጠይቃለሁ፡፡
ኤች አይቪን ለመግታት፣ ዓለም አቀፋዊ ትብብር፣ የጋራ ሃላፊነት!
አመሰግናለሁ፡፡

Alarm: