የክብርት ወ/ሮ አልማዝ መኮንን ንግግር

ክብርት ዶ/ር ሊያ ከበደ የጤና ሚ/ር ሚንስትር፣ የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂዎች፣ ክብርት ዶ/ር ጽጌረዳ ክፍሌ የፌደራል ኤችአይቪ/ኤድስ መከ/መቆ/ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር፣ የተከበሩ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ በኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የጉባዔው ጠቅላይ ፀሀፊ፣ የኤችአይቪ/ኤድስ መከ/መቆ/ቦርድ አባላት፤ የአጋር ድርጅቶችና የሲቪክ ማህበራት ኃላፊዎች፣ በዚህ ሀገራዊ ትልቅ የምክክር ጉባኤ ላይ የተገኛችሁ ክቡራትና ክቡራን፣ በመድረኩ ለነበራችሁ ተሳትፎና አስተወጽዖ፣ በቅድሚያ በራሴና በኢፌዴሪ በሰላም ሚኒስተር ስም ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያ፣ ባለፉት ጥቂት በማይባሉ ዘመናት፣ በበርካታ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች ውስጥ በማለፍ፣ በሁሉም ዘርፍ አመርቂ የሆኑ ውጤቶችን በማስዝገብ፣ የሚታዩ፣ የሚጨበጡ ውጤቶች የተመዘገበባት ቢሆንም ዛሬም ቢሆን ያልተሻገርናቸው ተግዳሮቶች ብዙ ናቸው፡፡ በተለይም በዛሬው ዕለት ውይይት ያደረግንበት ኤች አይቪ ኤድስ፣ ሶስት አስርት አመታትን የተሻገረ የጤና፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ተግዳሮት ነው፡፡
ባለፉት ዓመታት፣ የሀይማኖት ተቋማትና መንፈሳዊ አባቶች፣ ኤች አይቪ/ኤድስ እንደ ሀገር የሚያስከትለውን ዘርፈ ብዙ ችግሮች በውል በመረዳት፣ በሙሉ አቅማቸውና በከፍተኛ ቀርጠኝነት ባደረጉት ርብርብም ይደርስ ከነበረው የከፋ ችግር ሀገራችንን ታድገዋል፡፡ በየእምነት ተቋማቱ መዕመኑን በማስተማር፣ ወላጆቻቸውን በኤድስ ያጡ ህጻናትን በማሳደግ፣ ጧሪ ያጡ አረጋዊያንን በመንከባከብ፣ የኤድስ ህሙማንን ቤት ለቤት በመጎብኘትና በመደገፍ፣ መድሀኒታቸውን የሚያቋርጡትን ወገኖች እንዳያቋርጡ በመምከር፣ በገንዘብ፣ በቁሳቁስ፣ በስነ ልቦና ግንባታ መጠነ ሰፊ ተሳትፎ በማድረጋቸው ሀገራችንን እንደ ሀገር አስቀጥለዋል፡፡
ይሁን እንጂ ካፉት አስር ዓመታ ወዲህ በተገኘው ትልቅ ሀገራዊ ድል በመርካትና በመዘናጋታችን፣ በተለይም ወጣቱና ነገ ይችን ሀገር እንደ ሀገር የሚያስቀጥለውን አምራችና የሰላሟ አለኝታ የሆነውን ሀይል በኤድስ እየተነጠቅን እንገኛለን፡፡ በዚህም ምክንያት ከማህበራዊ ቀውሱ፣ ከስነ ልቦና ስብራቱ፣ ከድህነትና እንግልቱ ዜጎቻችንን በመታደግ ረገድ ያልሰራናቸው ስራዎች መኖራቸውን እንረዳልን፡፡
በመሆኑም ስንተባበር የማንፈታው ችግር፣ የማንሻገረው ዳገት የማንወጣው ተራራ አይኖርም፤ ህልውናችን የተሳሰረ፣ አንዱ በአንዱ ላይ የተመረኮዘ፤ ያልተነጣጠለና የጋራ ፍላጎትና እሴቶች ያሉን ህዝቦች ነን፡፡ ሁላችንም የሰላም ቤተሰቦችና በመተባበር፣ በአንድነትና ኤች አይቪ/አኤድስ ያስከተለብንን ማህበራዊ ችግር በመመከት የዚህ ትውልድ ባለአደራዎች ነን፡፡ በመደጋገፍ መስራት ሀገራችንንና ህዝቦቿን የምንታደግበት አይነተኛ መንገድ ነው፡፡
ኤች አይቪ/ኤድስ በባህሪው ዘርፈብዙ ምላሽ የሚያስፈልገውና የሁሉንም ባለድርሻ አካል የማይተካ ሀላፊነት ይጠይቃል፡፡ የኃይማኖት ተቋማትና አባቶች እስከታችኛው መዋቅር የሚወርድ ጠንካራ ምላሽ በመስጠት፣ የፀረ-ኤችአይቪ ሕክምና የጀመሩ ሰዎች እንዳያቋርጡ ተገቢና ትክክለኛ መረጃ በማስተላለፍ፣ በየቤተ ዕምነቱ ሰዎች ለኤችአይቪ እንዳይጋለጡ ትምህርትና አባታዊ ምከር በማስተላለፍ፣ ወቅቱ የኮሮና ወረርሽኝ በመሆኑ በኤችይቪ ምክንያት ይበልጥ ተጎጅ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች የበለጠ ትኩረት እንዲሰጣቸው በማድረግ በኩል የተጠናከረ ስራ መስራት ይጠበቅብናል፡፡
በመጨረሻም ኤድስ የማህበረሰብ የጤና ችግር እንዳይሆን ለማድረግ በሚደረገው አገራዊ ርብርብ፣ የሀይማኖት ተቋማትና መንፈሳዊ አባቶች ከመቼውም ዘመን ይልቅ ትልቅ ድርሻና ሀላፊነት ያላችሁ በመሆኑ፣ እጅ ለእጅ ተያይዘን፣ በአንድነትና በአብሮነት፣ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የተጀመረውን ዘርፈ ብዙ ስራ በመደገፍና ተቋማዊ፤ መንፈሳዊና አባታዊ ሃላፊነት በመወጣት፣ ትውልድ እንድታስቀጥሉ፣ ሀገር እንድትገነቡ፣ የአደራ መልዕክቴን አስተላለፋለሁ፡፡
ማህበረሰብ የለውጥ አቅም ነው!
አመሰግናለሁ!

አ አ የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ
መስከረም 12፣ 2013

Alarm: