ጾታዊ ጥቃትን የማይቀበል ማህበረሰብ ለመፍጠር ትውልድ ላይ መስራት ተገቢ መሆኑ ተገለፀ

የፌዴራል ኤችአይቪ/ኤድስ መከ/መቆ/ጽ/ቤት ሰራተኞች አለም አቀፍ የጸረ-ጾታዊ ጥቃት ቀንንና የጸረ-ሙስና ቀንን ህዳር 26 /2013 ዓ.ም በአዳማ ከተማ አክብረዋል፡፡
የዘንድሮው የጸረ-ሙስና ቀን የትውልድ ስነ-ምግባር ግንባታን በጠንካራ ዲሲፕሊን በመምራት ሌብነትንና ብልሹ አሠራርን በመታገል የብልፅግና ጉዞዓችንን እናፋጥን በሚል መሪ ቃል በአገር አቀፍ ደረጃ ለ17ተኛ ጊዜ እየተከበረ ይገኛል፡፡ አቶ ካይሩ ሁሴን በአለርት ሆስፒታል የጸረ-ሙስና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በዓሉን በማስመልከት ባስተላለፉት መልዕክት የሙስና ወንጀል አፈፃፀም ውስብስብና በከፍተኛ ጥንቃቄ የሚፈፀም ወንጀል በመሆኑ የወንጀሉን ፈፃሚዎች ለማግኘት የሚደረገው የምርመራ ሂደት ፈታኝና እልህ አስጨራሽ ነው ያሉ ሲሆን የሙስናን ወንጀል ከማጋለጥ አንጻር ሁሉም አካላት የራሳቸውን ድርሻ መወጣት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል በዕለቱ የጽ/ቤቱ ሰራተኞች በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን የማይታገስ ትውልድ እንፍጠር በሚል መሪ ቃል ህዳር 16 በአገር አቀፍ ደረጃ ለ15ተኛ ጊዜ የሚከበረውን የጸረ-ጾታዊ ጥቃት ያከበሩ ሲሆን ዕለቱን በማስመልከት በጤና ሚ/ር የሴቶችና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት ወ/ሪት ትሁት አየለ የነጭ ሪቫን ምልዕክትን ለመጠቀም ምክንያት የሆነው በሴቶች ላይ የሚፈፀመው ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች እንደሆኑ ተናግረው ወንዶች ሴቶች ላይ ጥቃት አላደርስም በማለት የነጭ ሪቫን አድርገው ንቅናቄውን መቀላቀል እንደጀመሩ ገልጸዋል፡፡
ዶ/ር ጽጌሬዳ ክፍሌ የፌዴራል ኤችአይቪ/ኤድስ መከ/መቆ/ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር ዛሬ ምናከብራቸው ሁለቱም በዓላት መሪ ቃሎች ትኩረት የሚያደርጉት የህብረተሰቡን ስነልቦና ከማነፅ ጋር ግንኙነት ያላቸው ስለሆኑ የጽ/ቤቱ ሰራተኞች የማህበረሰቡን ስብዕና ከመቅረፅ አኳያ የራሳቸውን ድርሻ መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
በአለም አቀፍ ደረጃ ከሶስት ሴቶች ውስጥ አንዷ በህይወት ዘመኗ በቅርብ አጋሯ ወሲባዊ ወይም አካላዊ ጥቃት ይደርስባታል፡፡

Undefined
Posted on: 
Monday, December 7, 2020
Alarm: 

Add new comment